ስለ ፊልሙ
ጥቂት ስለ ፊልሙ
ግርማዊ የታላቁን ንጉሠ ነገሥት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ሕይወት፣ ዘመን እና ታሪካዊ ቅርስ የሚዳስስ የፊልም ፕሮጀክት ነው። ፊልሙ ርዕሰ ጉዳዩን እንደ አንድ የፖለቲካ ሰው ብቻ ሳይሆን፣ ዘላቂነትን፣ የለውጥ ሂደትን፣ አነጋጋሪነትንና ታሪካዊ ፋይዳን ተምሳሌት አድርጎም ይመለከታል።
ዓለማችን በታላቅ የለውጥ ሂደት በነበረችበት በዚያ ዘመን ላይ የሚያተኩረው ይህ ፕሮጀክት፣ የቅኝ ግዛት መስፋፋት፣ ዲፕሎማሲ፣ ዘመናዊነት፣ የአፍሪካ ነጻነት እና ዓለም አቀፋዊ የኃይል አሰላለፍ በተቀያየረበት ዓለም ውስጥ የመሪነት ሚና ያለውን ውስብስብነት ይዳስሳል። ተመልካቾችም የአንድን መሪ ገጽታ፣ ውሳኔዎች እና ቅርሶች ዘመን ተሻግረው ዛሬም ድረስ ማስተጋባታቸውን እንዲያጤኑ ይጋብዛል።
ይህ ማለት ግን ያለፉ ነገሮችን ዝም ብሎ መተረክ አይደለም። ትዝታን፣ ሃገር የመምራት ብቃትን እና ማንነትን በዓይነ ኅሊና የሚያሳይ፣ በስሜት የተቃኘ እና ታሪካዊ ጥልቀት ባለው መልኩ በጥበብ ለመመርመር የተደረገ ጥረት ነው።
አንኳር ሐሳብ
ግርማዊ ስሙ በአህጉራት ሁሉ የገነነ፣ በዓለም አቀፍ ውጥረት፣ በአፍሪካ መነቃቃት እና በብሔራዊ የለውጥ ወቅት የደመቀ ታሪክ ያለውን የሀገር መሪ ሥራና ሕይወት ይተርካል። ፊልሙ ሀገር የማስተዳድርን ኃላፊነት፣ የመሪነትን ትርጉም፣ እንዲሁም በታላቅነት እና በባይተዋርነት መካከል ያለውን ቀጭን መስመር በድራማ እና በሲኒማዊ ትረካ ይዳስሳል።
ታሪኩ ሲገለጥ፣ ተመልካቾች በምኞት፣ በዲፕሎማሲ፣ በተቃውሞ፣ በአክብሮት እና በለውጥ ከተቀረጸ ዓለም ጋር ይፋጠጣሉ። ፊልሙ ቅርስ እንዴት እንደሚገነባ፣ እንዴት እንደሚፈተን፣ እና በሀገራት እና በትውልዶች ትዝታ ውስጥ ሕይወት ዘርቶ እንዴት እንደሚኖር ማሰላሰያም ነው።
ግርማዊ ስለ አንድ ሰው ብቻ ሳይሆን ስለ አንድ ሕዝብ፣ ስለ አንድ ዘመን፣ እና ዛሬም ድረስ ከፍተኛ ትርጉም ስላለው ታሪካዊ ቅርስና ውርስ የሚተርክ ፊልም ነው።
የፊልሙ ርዕይ
ግርማዊ ጥልቀት ያለው፣ እውነተኛውን ድባብ መፍጠር የሚችልና ውስጣዊ ስሜትን ከብስለት ጋር አዋህዶ የሚቀርጽ ፊልም እንዲሆን ታቅዷል። ግቡም ደረቅ የታሪክ ማጠቃለያ ላይ መድረስ ሳይሆን፣ ለውስጣችን ቅርብ የሆነ፣ የተከበረ እና ከዓይነ ኅሊናችን የማይጠፋ ሲኒማዊ ተሞክሮ መፍጠር ነው።
የታሪኩ አቀራረብ በተቃርኖዎች ላይ የተመሠረተ ነው፦ ግርማ ሞገስ እና ባይተዋርነት፣ ክብረ በዓል እና ጸጥታ፣ የሕዝብ እይታ እና የግል ሸክም፣ ድል አድራጊነት እና መንታ መንገድ ላይ መሆን። በጥንቃቄ በተቀረጹ ምስሎች፣ ድምጾች፣ ትረካዎች እና በብቁ ባለሙያዎች ትወና፣ የጉዳዩን አፈ-ታሪካዊ እና ሰብዓዊ ገጽታዎች በማሳየት ፊልሙ የተነሳበትን ዓላማ ለማሳካት ይጥራል።
ይህ ፕሮጀክት ታሪክ መብራራት ብቻ ሳይሆን ውስጣችን ድረስ ዘልቆ መግባት አለበት በሚል እምነት የሚመራ ነው። በተጨማሪም ፊልሙ ትተነው የምናልፈው ቅርስ ረቂቅ ነገር ሳይሆን ሕያውና የተፈተነ፣ በትዝታም ሆነ በታሪክ ምዕራፍ ሲታወስ የሚኖር መሆኑን ታዳሚዎች እንዲገነዘቡት ያደርጋል።
ዕይታ
ግርማዊ በታሪክ፣ በሥነ-ጥበብ እና በባህላዊ ትዝታ መጋጠሚያ ላይ የሚቆም የፊልም ፕሮጀክት ነው። ከፊልም አቅርቦት ባሻገርም ታሪክን የመጠበቅ፣ የመተርጎም፣ እና በሲኒማዊ ጥበብ የመተረክ ዘላቂ ፋይዳ ያለውም ነው።
ይህ ፕሮጀክት አንድን ታላቅ የታሪክ ሰው እና ዘመኑን ከነሙሉ ክብሩ፣ ገጽታውና ጥልቀቱ በአዲስ የእይታ ጥበብ በማምጣት፣ ለዘመናዊ ተመልካቾች ተደራሽ ለማድረግ ያለመ ነው። ነባር ወግና ሥርዓቱን እንዲያከብሩና እንዲነጋገሩበት፤ እንዲሁም ያለፈውን እና የአሁኑን ዘመን የሚያገናኝ ድልድይ እንዲገነቡ ይጋብዛል።
በአጠቃላይ ግርማዊ የሚመራበት ትልቅ ዓላማ አለው። ይኸውም የተሻለ ታሪካዊ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ፣ ባህላዊ ኩራትን የሚያጎናጽፍ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም መነጋገሪያ የሚሆን፣ እና ዘላቂ የጥበብ አሻራ ለመተው የሚችል ፊልም መሥራት ነው።
ታሪካዊ ዳራ
ግርማዊ ለሥራው መነሻ ያደረገው ዓለም በታሪካዊ ኃይሎች የተቃኘ ነበር። ኢትዮጵያ በአፍሪካ እና በዓለም መድረክ ልዩ ቦታ ነበራት። ጥንታዊ ሉዓላዊነቷን ይዛ ከዘመናዊው ዓለም በሚመጡባት ግፊቶች እየተፈተነች ነበር። ዘመኑ የተለዋወጡ ጥምረቶች፣ አዳዲስ የፖለቲካ እውነታዎች እና በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ እየጨመሩ የመጡ ተስፋዎች የታዩበት ነበር።
የቅኝ ግዛት፣ የዘመናዊነት፣ የነጻነት፣ የዲፕሎማሲ እና የብሔራዊ ማንነት ጥያቄዎች እጅግ በተቆላለፉበት ወቅት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዓለም አቀፋዊ መሪ ሆነው ብቅ አሉ። ተጽዕኗቸውም ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች በግልጽ ታይቷል።
ይህንን ዳራ መረዳት ፊልሙን ለመረዳት በእጅጉ ጠቃሚ ነው። ግርማዊ በታሪክ ላይ የተመሠረተ ጥበባዊ ሥራ ነው፤ ሆኖም ታሪክ በእውነታዎች ብቻ ሳይሆን በተምሳሌቶች፣ በታሪኮች እና በሕዝቦች ሕይወት ውስጥ የሚኖር ስሜት ጭምር መሆኑን ይገነዘባል።
ፊልሙ ለምን አስፈለገ?
ምክንያቱ ግልጽ ነው። አንዳንድ ታሪኮች ተበታትነው እንዳይቀሩ፣ በዝምታ እንዳይታለፉ፣ እና ከተራ ስም ማጥፋት እንዲጸዱ ማድረግ በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ነው። የምንጋራው ቅርስና ትሩፋት ከሃገራችን ታሪክ የዘለለ ፋይዳ እንዳለው መረዳት የግርማዊ ዋና መርሕ ነው። ይህም የአፍሪካ አኅጉርን፣ የአመራር ጥበብን፣ ታሪክን እና የወል ትዝታዎቻችንን ሰፋ ባለ መንገድ እንድንመለከት ይጠቅመናል።
ይህ ታሪክ ለብዙዎቻችን ክብርን፣ መንግሥትነትን፣ ዲፕሎማሲን፣ ጽናትን እና ባህላዊ ማንነትን ይወክላል። ለሌሎቻችን ደግሞ ሥልጣንን፣ ኃላፊነትን እና የታሪካችንን የለውጥ ሂደት የተመለከቱ ፈታኝ ጥያቄዎችን ያስነሳል። ይኸው የታሪካችን ውስብስብ ገጽታም ነው ደረጃው ከፍ ባለ የሲኒማ ጥበብ ሊገለጽ የሚገባው።
ግርማዊ ይህንን ታላቅ የታሪክ ምዕራፍ ለመጠበቅ፣ ለመመርመር እና ለተከታታይ ትውልዶች በዘላቂነት ለማስተዋወቅ ይሻል። ይህ ፊልም ትዝታንም ዘላቂ ፋይዳንም አጣምሮ የያዘ ነው። የታሪክ ቅርስና ውርስ ምን ማለት እንደሆነ እየዘከረ ለዛሬ ሕይወታችን ያለውን ፋይዳም ያነሳል።